ማክሰኞ:- ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም
ጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የ‹‹ስማርት ሲቲ›› ማሰልጠኛ ሆኖ ተመረጠ!!
ኮሌጁ በአውሮፓ ህብረት የኢራስመስ (Erasmus+) የገንዘብ ድጋፍ የሚደገፍና ዘመናዊ የከተማ ልማትን (Smart City) የሚያግዝ ታላቅ ፕሮጀክት መተግበር መጀመሩን አስታወቀ።
ኮሌጁ 10 ከሚሆኑ ሀገራዊ ተቋማትና ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለዘመናዊ ከተማ ልማት የሚሆን የሰው ኃይል በብቃት ለማፍራት የሚያስችል ስምምነት አድርጓል።
ይህ ፕሮጀክት በጋራ ጥምረት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉን ዕድገትና ተግዳሮት የሚፈቱ ጥናትና ምርምር በመስራት፣ ፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ለዘርፉ አሰልጣኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የገበያውን ፍላጎትና የአለም አቀፍ ደረጃን ያገናዘበ የካሪኩለም ቀረፃ ሃላፊነቱን በመወጣት፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናው ጥራትና ውጤታማነት በሳይንሳዊ መንገድ መመራቱን በመቆጣጠር የሚሳተፉ ሲሆን ጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተቀረፀው ካሪኩለም መሰረት ስልጠናውን በተግባር በመስጠት የፕሮጀክቱ ዋና አካል ይሆኗል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በአጫጭር ስልጠናዎች የሚጀምር ቢሆንም በቀጣይ ወደ ደረጃ የስልጠና መርሃ-ግብር ለማሳደግ ስትራቴጂያዊ እቅድ ተይዟል።
ይህ እርምጃ አዲስ አበባ የጀመረችውን ‹‹ስማርት ሲቲ›› ጉዞ የሚያስቀጥል፣ በቴክኖሎጂ የዳበረ እና ለስራ ገበያው ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ይህንን ዓለም አቀፍ ዕድል ማግኘቱ ተቋሙ በዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚያሳይ ነው።
በተጨማሪም የአሰልጣኞች እውቀትና ክህሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፣ ዘመናዊ የስልጠና መሳሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ግብዓት በማሟላት እና የሚሰጠው ስልጠና የተግባርና የምርምር ውጤት በመሆኑ ለሰልጣኞች በቀጥታ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ለኮሌጁ እንደ ትልቅ ዕድል ተቆጥሯል።


.